በሙያ ስራ ላይ ለተሰማሩ የህግ ታራሚዎች የክህሎት ማረጋገጫ ስልጠናና እውቅና ለመስጠት የሚያስችል የውይይት መድረክ ተካሄደ





Executive Abstract
""
የሐረሪ ማረሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የህግ ታራሚዎችን ለነገው ህይወታቸው በማዘጋጀትና ወደ ማህበረሰቡ በብቃት እንዲቀላቀሉ ለማስቻል እየተከናወነ ያለውን የሪፎርም (የእርምት) ስራ አጠናክሮ ቀጥሏል።
የዚህ ስራ አካል በሆነውና በተለያዩ የልማት መስኮች በተለይም በጀጎል ኮሪደር ግንባታ ላይ በተግባር ስራ ላይ ለተሰማሩ ታራሚዎች የአጭር ጊዜ ስልጠና በመስጠት የክህሎት ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት ለማበርከት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ዛሬ ሰፊ የጋራ ውይይት ተደርጓል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የሐረሪ ማረሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አድናን አህመድ እንደገለጹት፣ የታራሚዎችን የእርምት ቆይታ ውጤታማ ለማድረግና ከማረሚያ ቤት ሲወጡ በሰለጠኑበት ሙያ ተሰማርተው ራሳቸውንና ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ ለማስቻል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል።
ኮሚሽነሩ አክለውም፣ የታራሚዎቹን የተግባር ልምድ በንድፈ-ሀሳብ በማጠናከር ሰርቲፋይ የማድረጉ ሂደት በፖሊቴክኒክ ኮሌጆችና በሚመለከታቸው የዘርፍ ተቋማት አማካኝነት የሚከናወን መሆኑን ጠቁመዋል።
የመድረኩ አስተባባሪና የተሃድሶ ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮማንደር አብራሂም ዑመር በበኩላቸው፣ ይህ የተቀናጀ አሰራር ታራሚዎች ያላቸውን ክህሎት ወደ ተቀመጠው የሙያ ደረጃ (Standard) በማምጣት፣ ወደ ማህበረሰቡ በሚቀላቀሉበት ወቅት የስራ ዕድል በቀላሉ እንዲያገኙ ለማድረግ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል።
© 2026 Harari Prison Police Commission • All Rights Reserved
